ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ገስጥ ተጫኔ የአፍሪካ ምርጥ 78 የሕግ ባለሞያዎች ዝርዝር ውስጥ ገባች

መስከረም ገስጥ ከትምራን መሥራች አባላት መካከል አንዷ ስትሆን፣ የሲቪክ ማኅበሯ የቦርድ ሰብሳቢ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች።
መስከረም በሕግ ሞያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ከፈጠሩ አፍሪካውያን ሴቶች መካከል አንዷ ሆና በመመረጧ ትምራን እንኳን ደስ አለሽ ትላለች።
በቀጣይም ትልልቅ ስኬቶች እንደምታስመዘግብ ትምራን ሙሉ እምነት አላት።

ከዕዝራ  እጅጉ 

“ኮርትሩም ሜል” የተሰኘ የሕግ ባለሞያዎችን ሥራ የሚያስተዋውቅ ዲጂታል መጽሔት ከሰሞኑ የ78 ሴት አፍሪካውያን የሕግ ባለሞያዎችን ዝርዝር ከእነ ግለ ታሪካቸው አውጥቷል። 

ይህ ዲጂታል መጽሔት በአፍሪካ የታወቀ ሲሆን፣ 100 ሴት ጀግኒት የሕግ ባለሞያዎችን እውቅና እየሰጠ መዝለቁ የበለጠ ከበሬታን አስገኝቶለታል።   

የሕይወት ታሪካቸው በዲጂታል መጽሔቱ ላይ ከተሰነደላቸው መካከል ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ገስጥ ትገኝበታለች። በሕግ ሞያ ላይ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ የፈጠሩ ሴት ባለሞያዎችን ወደ አንባቢያን የሚያደርሰው ይህ ተቋም በይፋ ከተመሠረተ 5 ዓመቱን ያስቆጠረ ሲሆን፣ መሥራቹም አንቶኒ አታታ የተባለ ታዋቂ አፍሪካዊ የሕግ ባለሞያ ነው።

መሥፈርቱን የሚያሟሉ ሴት የሕግ ባለሞያዎችን በመምረጡ በኩል ሞያዊ ድርሻቸውን ለመወጣት የፈቀዱ 23 ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ባለሞያዎች የተሳተፉ ሲሆን ፣ ኬንያዊቷ እውቅ የሕግ ባለሞያ ማሪያ ቤኔካ የዳኞቹ ሰብሳቢ ናቸው።

ዳኞቹ የመምረጥ ተግባሩንም በጥንቃቄ እንደተወጡ ለማወቅ ተችሏል። አዘጋጅ ኮሚቴው 100 ባለሞያዎችን ለይቶ የማውጣት እቅድ ቢኖረውም ከሁሉም ሀገራት መስፈርቱን የሚያሟሉ በቂ ዕጬዎች ባለመገኘታቸው 78ን ብቻ ይፋ አድርጓል። አምና ከነበረው የባለሞያዎች ቁጥርም የዘንድሮው መጨመሩንም ዝግጅት ክፍሉ በዲጂታል መጽሔቱ ላይ አስታውቋል።

የዓለም የሴቶችን ቀንን (ማርች 8) ምክንያት በማድረግ ይፋ የሆነው ይህ ዝርዝር በዲጂታል መጽሔቱ ላይ የባለሞያዎቹን ታሪክ ያወጣው በያዝነው መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

78ቱ ሴት የሕግ ባለሞያዎች ልምድ እና እውቀት ያካበቱ በመሆናቸው በዝርዝር ውስጥ ስማቸው መካተቱ ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል ሲልም ኮሚቴው ሐሳቡን አስፍሯል።

የሕይወት ታሪካቸው ከሰፈረላቸው አፍሪካውያን መካከል ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ገስጥ ተጫኔ ባለፉት 20 ዓመታት በአገር አቀፍ፣ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰብአዊ መብት ላይ ጉልህ ሚና ያበረከተች በሳል ባለሞያ ናት።

በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት  ከፍተኛ  ባለሞያ ወይም ልዩ ልኡክ፣ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር፣ ዳኛ፣ ጠበቃ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት መሪ፣ የሕግ መምህር በመሆን ያገለገለች ሲሆን ለዚህም በቂ ዕውቅና ተችሯታል።

መስከረም ገስጥ፣ በተለይም በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እና መድልኦዎች እንዲወገዱ ጉልህ ሚና ተጫውታለች።

ከሁለት ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር ሆና ባገለገለችበት ወቅትም የሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ ምርመራ እና ስነዳ ሥራዎችን መርታለች። በተለይም በሀገሪቱ አለመረጋጋት እና ግጭቶች በተበራከቱበት አስቸጋሪ ወቅት ከጦርነት ጋር በተያያዘ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን አስመልክቶ አስፈላጊውን መረጃ የማጠናቀር እንዲሁም ይፋ የማድረግ ሓላፊነቷን ለመወጣት የቻለች ባለሞያ ናት።

ይህች ኢትዮጵያዊት የሕግ ባለሞያ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባለሞያነት የስድስት ዓመታት የአገልግሎት ዘመኗ የባለሞያዎች ቡድኑ ሰብሳቢም ሆና የሠራች ሲሆን፣ በተለያዩ አህጉራት የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን  ለመከታተል፣ ለመዘገብ እና በሚመለከታቸው አካላትና በተመድ ምላሸ‍ እንዲያገኙ ጥረት ለማድረግ ችላለች። በአፍሪካ ኅብረት የሰብአዊ መብቶች ተቋማትም ጋር በባለሞያነት በቅርበት ሠርታለች። ለበርካታ የአፍሪካ የሕግ ባለሞያዎች እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ሥልጠና እና ድጋፍ በማድረግም አህጉራዊ አስተዋጽኦዋን አበርክታለች።

መስከረም የመጀመሪያ ዲግሪዋን በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪዋን ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ በሰብአዊ መብቶች እና ዴሞክራሲ ያገኘች ሲሆን፣ የፒኤችዲ ዲግሪዋን ደግሞ በፓዶቫ ዩኒቨርሲቲ በመከታተል ላይ ትገኛለች።

በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ርእሰ ጉዳዮች ላይ በተለይም በሴቶች እና በሕፃናት መብቶች፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መብቶች፣ የልማት መብቶችና ግቦች፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን ያሳተመችው መስከረም በአፍሪካ፣በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ተጋባዥ መምህር በመሆን አገልግላለች።

መስከረም ገስጥ ተጫኔ በዚህ አስተዋጽኦዋ እንደምትቀጥል ትናገራለች።

https://www.courtroommail.com/breaking-news-2025-courtroom-mail-100-released-kenya-south-africa-dominate-list
Share this post on