info@timran.et | +251 116 73 48 48
በሴቶች መብቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች የተሳተፉበት “ወደ 2018 የኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ” በሚል ጭብጥ ውይይት ተካሄደ


ትምራን ከናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዩት ባገኘችው የገንዘብ ድጋፍ ከኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር፣ ከኢትዮ አፍሪክ ኮንሰልቲንግ እና ሬይዚንግ እንዲሁም ከተመድ የሴቶች ድርጅት ጋር በመተባበር በሴቶች መብቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች የተሳተፉበት “ወደ 2018 የኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ” በሚል ጭብጥ ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም በኢንተርሌግዥሪ ሆቴል የውይይት መድረክ አካሄደች።
የመድረኩ ዓላማ በሀገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል እና የፖለቲካ ተዋናዮች ምላሽ ሰጭ መንግሥት እንዲኖር ለማስቻል የሚያደርጉትን ተሳትፎ መጨመር ነው።
በመድረኩ ላይ በሴቶች መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የምርጫ ቦርድ፣ የኢፌዴሪ ፓርላማ ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ፣ የሴት ፖለቲከኞች ጥምረት፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን፣ የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር፣ የተመድ የሴቶች ድርጅት ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።
በዚህም መሠረት:-
#በምርጫ ወቅት የሚፈጸሙ የሴቶች ጥቃቶች ምንነት ጽንሰ ሐሳቦች፣ አካሄዶች እና ምርጥ ተሞክሮዎች፣
#በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት የነበሩ ጥቃቶች ሁኔታ እና የሥርዓተ ጾታ ክፍተቶች ላይ የተገኙ ተሞክሮዎች፣
#በሴቶች መብቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ለምርጫ 2018 ያላቸው ዝግጅት እና ቅንጅት፣
#በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎች፣
#በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የመከታተያ መንገዶች እና ሂደቶች፣
#በምርጫ ወቅት ለሴቶች የሚሰጡ የጥበቃ እና ከለላ ዘዴዎች፣
#በጉዳዩ ላይ ለሚከናወኑ ተግባራት የሀብት ማሰባሰብ ስልቶች፣
#ለ7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ሥራ የጋራ የተግባራት፣ የሚና፣ የጊዜ እቅድ እና ችግሮችን የመግቻ ስልቶች የሚሉ ጭብጦች ላይ ገለጻ እና ውይይት ተካሂዷል።
ይህንን ስልታዊ ተግባር የሚያቀናጅ የተለያዩ ድርጅቶችን ተወካዮች ያቀፈ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተዋቅሯል።
ትምራን የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ እና ውሳኔ ሰጭነት ሚና የማሳደግ ራእይ ሰንቃ ከአምስት ዓመታት በፊት የተቋቋመች ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበር ነች።
#ምርጫ2018