info@timran.et | +251 116 73 48 48
ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በሁለት ዓመታት ቆይታ ያከናወናቸውን ተግባራት የሚያሳይ የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ከተቋቋመበት መጋቢት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያከናወናቸውን ዋና፣ ዋና ተግባራት የተመለከተ የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ።
ውይይቱ የተካሄደው የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት በየሳምንቱ በሚያዘጋጀው ሥርዓተ ጾታ ተኮር /Gender in Focus/ የበይነ መረብ መድረክ ላይ ነው።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጥምረቱ ጽ/ቤት የኾነችው ትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን ተከትሎ ሴቶች በኮሚሽኑ ውስጥ በተገቢው መልኩ እንዲካተቱ ብሎም በምክክሩ ሂደት ውስጥ ትርጉም ባለው ሁኔታ እንዲሳተፉ ለማስቻል 22 ሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች እና የሴቶች ማኅበራት ተሰባስበው ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክን ከሁለት ዓመታት በፊት መመሥረታቸውንና በሂደቱም ወስጥ የተሳካ ጉዞ እንደነበረው ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት ጥምረቱ ከስምንት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ያሰባሰባቸውን የሴቶች አጀንዳዎች አደራጅቶ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማስረከብ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የጥምረቱ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ ደግሞ ጥምረቱ ያከናወናቸውን ዋና፣ ዋና ተግባራት አብራርተዋል። ከእነዚህም መካከል:-
- ከ12 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ 151 ሴቶች የአሠልጣኞች ሥልጠና መስጠቱን፣
- በስምንት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረሪ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ሀገራዊ ምክክርን በተመለከተ ለ4005 ሴቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት አጀንዳዎቻቸውን በመሰብሰብ እና በማጠናቀር ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማስረከብ ዝግጅት ላይ መሆኑን፣
- ከኢትዮጵያ ሴት አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበር ጋር በመተባበር አካል ጉዳተኛ ሴቶች እና ሀገራዊ ምክክር ውስጥ ማካተት ላይ ያተኮሩ ሁለት ሥልጠናዎች መስጠቱን፣
- ኢንክሉሲቭ ፒስ ከተሰኘ መያድ ጋር በመተባበር ለጥምረቱ አባላት የሴቶች አጀንዳዎችን ከሥርዓተ ጾታ አኳያ መቃኘት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች ማዘጋጀቱን፣
- የሴቶችን ተሳትፎ ለመጨመር እንዲቻል ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተገኘባቸው መድረኮች ሐሳቦችን በማንሸራሸር ኮሚሽኑ ለሴቶች ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉን፣
- የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አባል እና አጋር በመሆን የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች መሥራቱን፣
- ከልዩ፣ ልዩ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ሴቶች ማኅበራት ጋር ትስስር በመፍጠር የአባል ድርጅቶችን 56 ማድረስ መቻሉን፣
- ከበርካታ ባለድርሻ አካላት፣ አጋሮች እና ለጋሾች ጋር አብሮ በመሥራት በዋናነት ከዩኤስኤይድ/ኤንዲአይ እና አይሪሽ ኤይድ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ከፍሬደሪክ ኤቨርት ስቲፍተንግ፣ ኢንክሉሲቭ ፒስ እና ኦቲአይ የቴክኒክ ድጋፍ በማግኘት በክልሎች ሥልጠናዎች መስጠቱን፣
- ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ተከታታይ የማኅበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ ዘመቻዎች ማከናወኑን፣
- ጥምረቱ የአሠልጣኞች ሥልጠና ከሰጣቸው 151 ሴቶች መካከል ከ20-30 በመቶ የሚሆኑት ኮሚሽኑ በየክልሎች ባካሄዳቸው ምክክሮች ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን፣
- ጥምረቱ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በመተባበር በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ አባል ድርጅቶቹ የተሳታፊ ልየታ ላይ ተባባሪ አባል ሆነው እንዲሠሩ ማድረጉን፣
- የጥምረቱን የዕለት ተዕለት ሥራዎች በራሱ ማኅበራዊ ሚዲያ እና በጽ/ቤቱ ድረ ገጽ በስፋት ማስተዋወቁን፣
- ጥምረቱ በክልሎች ለሚያደርጋቸው ምክክሮች ያዘጋጀው የምክክር ማሠልጠኛ ሰነድ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሰባት ቋንቋዎች (አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማሊኛ፣ ሲዳምኛ፣ ሀድይኛ እና ወላይትኛ) ተተርጉሞ ሥራ ላይ መዋሉን ጠቅሰዋል።
ይህንን ተከትሎ ከተሳታፊዎች ጥያቄ የተነሣ ሲሆን፣ በጥምረቱ ጽ/ቤት በኩል ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቷል። የሴቶች አጀንዳ ልየታ ከተለመዱ ተሳታፊዎች ወጣ ባለ መልኩ ታችኛው ማኅበረሰብ ድረስ የሚደርሱ መስፈርቶችን በማውጣት መከናወኑን፣ ከስምንት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ተሰብስበው በአማካሪ የተጠናቀሩ የሴቶች አጀንዳዎችን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቅርቡ እንደሚያስረከብ፣ ከፍሬደሪክ ኤቨርት ስቲፍተንግ ባገኘው የ50 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶች ውይይቶችን እንደሚያካሂድ እና የሴቶች ምክክር ላልተከናወነባቸው አማራ፣ ትግራይ እና ጋምቤላ ክልሎች ደግሞ በጀት በማፈላለግ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
በቀጣይ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ 1000 ሴቶችን ለማሠልጠን፣ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ የውትወታ ሥራዎች ለመሥራት እና ለኮሚሽኑ የተሰጡ የሴቶች አጀንዳዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው የውትወታ ሥራዎች ለመሥራት መታቀዱ ተመልክቷል።
በመጨረሻም እነዚህ ሥራዎች ሲሠሩ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በጥምረቱ ባለሞያዎች ዘንድ ችግሮች መፍጠራቸውን፣ በቀበሌ ደረጃ በተሠሩ ሥራዎች ላይ የእስር ማስፈራሪያዎች ማጋጠማቸውን እና የመሠረተ ልማት ችግሮች ለሥራው ፈታኝ እንደነበሩ ተነሥቷል።