ጥምረት ለሴቶች ድምፅ የጋምቤላ ክልል የሴቶች ምክክር መድረክ የመክፈቻ መርሐ ግብር አከናወነ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወረዳ ደረጃ የሚያደርጋቸው የሴቶች ማኅበረሰብ አቀፍ ምክክሮች የመክፈቻ መርሐ ግብር ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም በጋምቤላ ከተማ ተከናወነ።

በምክክር መድረኩ ላይ ከክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች፣ የዞን እና ወረዳ መዋቅሮች የተወከሉ የሥራ ሓላፊዎች ተገኝተዋል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ሓላፊ ወ/ሮ አኬሎ ኦዋር ሀገራዊ ሰላምን ለማጽናት በሀገር ደረጃ መመካከር አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በመቀጠል የጥምረቱ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ጥምረቱ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በመጀመሪያ ምእራፍ በስምንት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ሴቶችን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማስረከቡን ጨምሮ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት አብራርተዋል።

በጋምቤላ ክልል የሚከናወኑት ማኅበረሰብ አቀፍ የሴቶች ውይይቶች አይሪሽ ኤይድ በሰጠው የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አቶ አስቻለው ያቀረቡትን ገለጻ ተከትሎ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች አንሥተው ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አፈ ጉባኤ አማካሪ የሆኑት አቶ ቦል ኞች የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር የተሳካ እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን በማለት ባስተላለፉት መልእክት መርሐ ግብሩ ተጠናቅቋል።

Share this post on