በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሴቶችን ሚና ለማጉላት ለሚካሄድ የውትወታ ተግባር የሚዲያ ሚና በሚል ጭብጥ የምክክርመድረክ ተካሄደ

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ከአይሪሽ ኤይድ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከኢትዮጵያ ሴት መገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎች ማኅበር ጋር በመተባበር በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሴቶችን ሚና ለማጉላት ለሚካሄድ የውትወታ ተግባር የሚዲያ ሚና በሚል ጭብጥ ለሚዲያ መሪዎች እና ባለሞያዎች የምክክር መድረክ ሚያዚያ 02 ቀን 2017 በአዳማ ከተማ አካሄደ።

በምክክር መድረኩ ላይ ሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ 30 ገደማ የመንግሥት እና የግል ሚዲያ ጋዜጠኞች፣ የኮሙዩኒኬሽን ባለሞያዎች፣ የሴት መብት ተሟጋች ጋዜጠኞች፣ ዩቲዩበሮች፣ የማስታወቂያ ባለሞያዎች እና ጸሐፊዎች ተገኝተዋል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጥምረቱ ጽ/ቤት የሆነችው ትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ጥምረቱ ያከናወናቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች ጠቅሰዋል።

በዋናነት ጥምረቱ መመሥረቱን ተከትሎ ሴቶች የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው እንዲመረጡ ማድረጉን፣ ሴቶች በምክክር ሂደት ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ተከታታይ የሕዝብ ማስታወቂያ ቅስቀሳ በመደበኛ እና ማኅበራዊ ሚዲያ ማሰራጨቱን፣ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሴቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች በስተቀር በሁለት ከተማ አስተዳደሮች እና ሁሉም ክልሎች በርካታ መድረኮች ማዘጋጀቱን፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚያካሂዳቸው መድረኮች የሴቶችን ተሳትፎ 30 በመቶ እንዲያደርግ የውትወታ ሥራ በመሥራት ውጤት ማስመዝገቡን፣ ከዐሥር ክልሎች የተሰባሰቡ የሴቶች አጀንዳዎችን በማጠናቀር ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማስረከቡን ጠቅሰዋል።

የጥምረቱ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ በበኩላቸው፣ ከጥምረቱ ራእይ፣ ተልእኮ እና ዓላማ ጀምረው በዝርዝር ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ ገለጻ አቅርበዋል።

በዋናነት ጥምረቱ ከመጋቢት 2015 ዓ.ም እስከ ሠኔ 2016 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ባካሄዳቸው መድረኮች ከ3500 በላይ የሴቶች አጀንዳዎች መሰብሰቡን፣ የሀገራዊ ምክክር ምንነት እና አተገባበር አስመልክቶ ለ6000 ገደማ ሴቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠቱን፣ ከዚያም በማእከላዊ ኢትዮጵያ እና ጋምቤላ ክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እና የማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች ማካሄዱን፣ የተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ሴቶች የምክክር መድረኮች ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

በመቀጠል የምክክሩ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች ያነሡ ሲሆን፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባካሄዳቸው መድረኮች የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው የሚል ዘገባ መጋቢት ወር ውስጥ ወጥቷል እንዴት ታዩታላችሁ? ሀገራዊ ምክክርን ጨምሮ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ መብት ቢሆንም ወደኋላ እየተመለሰ ስለሆነ ጥምረቱ ምን ሊሠራ አስቧል? ለሴቷ የሚያስፈልጋት አካታችነት ወይስ ጉዳዩዋ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን? በርካታ ችግሮች ባሉባቸው  አማራ እና ትግራይ ክልሎች ጥምረቱ እስከዛሬ ድረስ የሴቶችን ምክክር ያላደረገው ለምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎች ተነሥተዋል።

በምላሹም ጥምረቱ በቀጣይ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ የውትወታ ሥራዎችን ከሚዲያ አካላት እና ባለሞያዎች ጋር ለመሥራት ማቀዱን፣ የሴቶች አካታችነት የሚለው ለረጅም ጊዜ ተዘንግታ በመቆየቷ በሂደት የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ እንጂ በዚህ ብቻ የሚያቆም አለመሆኑን፣ አማራ እና ትግራይ ክልል ለመግባት አስቻይ ሁኔታ አለመኖሩንና በጀት ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተጠቅሷል።

በመጨረሻም የጥምረቱን ቀጣይ የውትወታ ሥራ አቅጣጫ የሀብት ማሰባሰብ እና የውትወታ ባለሞያ ኤልሳቤጥ ጌታቸው ያቀረቡ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች በኩል የጥምረቱን የውትወታ ሥራዎች ውጤታማ ለማድረግ ከሚዲያ ተቋማት ጋር ግንኙነት መፍጠር በተለይም መሪዎች ጋር ውይይት ማድረግ፣ ከጋዜጠኞች ጋር ተባብሮ መሥራት እና መንግሥት ለሴቶች ጉዳይ ከአካል ጉዳት ጋር የሚኖሩትን ጨምሮ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ ግፊት ማድረግ፣ የውስጥ የሚዲያ አቅምን መጠቀም የሚሉ ሐሳቦች ተሰንዝረው መድረኩ ተጠናቅቋል።

TIMRAN@5

Share this post on