info@timran.et | +251 116 73 48 48
በቀጣይ ጊዜ በሚደረገው ሀገራዊ ጉባኤ ላይ የሴቶች ተሳትፎ ጉልህ እንዲሆን ፍላጎት አለን-ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርአያ


ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በሁለተኛ ዙር ከሦስት ክልሎች ማለትም ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ እና አማራ ክልሎች እንዲሁም ከተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች እና ከፖለቲካ ፓርቲ አባላት ሴቶች የሰበሰባቸውን የሴቶች አጀንዳዎች ጥር 13 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጽ/ቤት በአካል ተገኝቶ አስረከበ።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርአያ፣ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ላለፉት ሦስት ዓመታት የሀገራዊ ምክክር ሥራዎችን በማገዝ ረገድ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥተዋል። በቀጣይ ጊዜ በሚደረገው ሀገራዊ ጉባኤ ላይ የሴቶች ተሳትፎ ጉልህ እንዲሆን ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል። በተለይም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች በተሳታፊነት፣ በአስተባባሪነት እና በአወያይነት የሚኖራቸው ተሳትፎ እንዲጨምር ኮሚሽኑ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንና ጥምረቱም የጉባኤውን ሂደት በማገዝ ረገድ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት አሳስበዋል።
ሀገራዊ ጉባኤ ለማድረግ ጫፍ ላይ እንገኛለን ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ጉዳዩን ለመቋጨት የሚቀረን የትግራይ ክልል ምክክር ብቻ ነው። ምክንያቱም ያለ ትግራይ ክልል ተሳትፎ ሀገራዊ ምክክሩ ሀገራዊ መሆን ስለማይችል፣ ይህንንም ለማድረግ ደግሞ የኮሚሽኑን ምክር ቤት ውሳኔ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።

በርክክቡ ላይ የተገኙት ኮሚሽነር ብሌን ገ/መድኅን በበኩላቸው፣ ጥምረቱ ሴቶች በሀገራዊ ምክከር ሂደት ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ለማስቻል ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነዋል። በቀጣይ ሀገራዊ ጉባኤ ላይ እንዲሁ በክትትል እና ግምገማ ረገድ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ብሎም ጉባኤው ሥርዓተ ጾታ ተኮር እንዲሆን በተሳታፊነት ሊወከሉ የሚችሉ ሴቶችን ወደፊት በማምጣት ረገድ ጥምረቱ ሥራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር ሳባ ገ/መድኅን፣ በሀገራዊ ጉባኤው ላይ የሴቶች ተሳትፎ በተለያዩ ምክንያቶች እንዳይቀንስ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ጠቅሰው፣ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በጥምረቱ አባል ድርጅቶች በኩል የውትወታ ሥራዎች የመሥራት እቅድ መኖሩን ተናግረዋል።