በፖለቲካ ተግባቦት እና የምርጫ ቅስቀሳ ክሂሎት ላይ ለትምራን ባለሞያዎች የተዘጋጀው የአሠልጣኞች ሥልጠና ተጠናቀቀ

የጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር የሲቪል ፒስ ሰርቪስ ከትምራን ጋር በመተባበር በፖለቲካ ተግባቦት እና የምርጫ ቅስቀሳ ክሂሎት ላይ ከመጋቢት 09-13 ቀን 2016 ዓ.ም ለትምራን ባለሞያዎች ያዘጋጀው የአሠልጣኞች ሥልጠና ተጠናቀቀ።

በሥልጠናው ላይ የፖለቲካ ተግባቦት ምንነት፣ ተዋናዮች እና መገለጫዎች፣ በምርጫ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አማካሪዎች እና ሚዲያ ሚና፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የማሳመን ጥበብ እና የፕሮፓጋንዳ ምንነት፣ መራጮች ዕጩዎችን ለመምረጥ አልያም ላለመምረጥ እንዲወስኑ የሚያደርጉ ምክንያቶች፣ ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው መራጮች መገለጫዎች እና ድምፅ ማግኛ መንገዶች፣ የምርጫ ቅስቀሳ ስልቶች እንዲኹም የኢትዮጵያ ምርጫ ዘመቻ የሕግ ማእቀፎች የሚሉ ጭብጦች ከተዳሰሱት መካከል ናቸው።

ሥልጠናውን ለአምስት ቀናት የሰጡት ዳንኤል ወርቁ ከገለጻ በተጨማሪ፣ የግል እና የቡድን ተግባራት፣ ተሞክሮዎች፣ ጥናቶች፣ ማሳያዎች፣ ሰነዶች፣ ንግግሮች፣ ምስለ ተግባራት፣ ጨዋታዎችን በማካተት ሠልጣኞች በንቃት እንዲሳተፉ አድርገዋል።

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለሠልጣኞች የእውቅና ምስክር ወረቀት የሰጡት የትምራን መሥራች አባል ብሌን ዐሥራት፣ ትምራን ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ሥልጠና ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተውጣጡ ሴት ፖለቲከኞች መስጠቷን አውስተው፣ ለባለሞያዎቿ መዘጋጀቱ በቀጣይ በውስጥ አቅም መሰል ሥልጠናዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ለመስጠት የሚያስችላት በመኾኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

አያይዘውም የሀገራችን ፖለቲካ እጅግ ፈታኝ ቢኾን እንኳን፣ ሴት ፖለቲከኞች ተግዳሮቱን ፈርተው እንዳይርቁ ለማስቻል ትምራን ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ማዘጋጀት እንደሚኖርባት አሳስበዋል።

በመጨረሻም ሠልጣኞች ከክብር እንግዳዋ ጋር የጋራ ፎቶ ተነሥተው መርሐ ግብሩ ተጠናቅቋል።

Share this post on

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *