በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሴቶች አጀንዳዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠንካራ የውትወታ ሥራ ያስፈልጋል-ሳባ ገብረ መድኅን

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሴቶች አጀንዳዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠንካራ የውትወታ ሥራ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር እና የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሳባ ገብረ መድኅን ገለጹ።

ሰብሳቢዋ ይኽንን ያሉት ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ከስምንት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ያሰበሰባቸውን የሴቶች አጀንዳዎች የማረጋገጥ ምክክር መድረክ ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባካሄደበት ወቅት ነው።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የትምራን ሥራ አስኪያጅ ኢየሩሳሌም ሶሎሞን፣ ለምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች እንኳን ደኅና መጣችኹ ካሉ በኋላ፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን ተከትሎ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሴቶች ትርጉም ባለው መልኩ እንዲወከሉ ለማስቻል ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ መጋቢት 2014 ዓ.ም መመሥረቱን አውስተዋል።
አያይዘውም ጥምረቱ የዕለት ተዕለት ሥራውን በሚከታተለው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መሪነት እና በጽ/ቤትነት በምታገለግለው ትምራን አማካኝነት የሴቶችን አጀንዳዎች ለማሰባሰብ እንዲቻል ከመላው ሀገሪቱ ለተውጣጡ 152 ሴቶች የአሠልጣኞች ሥልጠና መስጠቱንና ከመጋቢት 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ በስምንት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ባካሄዳቸው 54 መድረኮች በርካታ የሴቶች አጀንዳዎች መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።

በዚኽ ሂደት ውስጥ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረሪ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ሶማሊ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ከ4000 በላይ ሴቶች ሀገራዊ ምክክርን አስመልክቶ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።

ሥራ አስኪያጇ ከተጠቀሱት ስምንት ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተሰባሰቡ የሴቶች አጀንዳዎችን የማጠናቀር የአራት ቀናት መድረክ ግንቦት 2016 ዓ.ም ውስጥ መከናወኑንና በተቀጠረው አማካሪ ድርጅት አማካኝነት የተጨመቁ የሴቶች አጀንዳዎችን ለማረጋገጥ የዕለቱ መድረክ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

እነዚኽን ተግባራት ለማከናወን በርካታ አጋር ድርጅቶች እና ለጋሾች ከጥምረቱ ጎን እንደነበሩ አመልክተው፣ በተለይ አይሪሽ ኤይድ እና ዩኤስኤይድ/ኤንዲአይ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲኹም ፍሬደሪክ ኤቨርት ስቲፍተንግ ኢትዮጵያ፣ ኢንክሉሲቭ ፒስ እና ዩኤስ ኤይድ/ኦቲአይ ለሰጡት የቴክኒክ ድጋፍ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች የተቀረፁ የሴቶች አጀንዳዎች ላይ ወሳኝ ግብአት በመስጠት ንቁ ተሳታፊ እንደሚኾኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በመቀጠል የጥምረቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ድባቤ ባጫ ባደረጉት ቁልፍ ንግግር፣ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ለሴቶች አጀንዳዎች ትኩረት መስጠት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በዚኽ ሂደት ውስጥ ለተሳተፉ የጥምረቱ አባል ድርጅቶች፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ጽ/ቤቱ እና ሠራተኞች፣ ለጋሾች እና አጋሮች እንዲኹም በተለያየ መንገድ ለተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የሴቶች አጀንዳዎች ተጠናቅረው ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቀርቡ ለማድረግ የተቀጠረው ቲቢ አማካሪ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ተሾመ በየነ፣ የአጀንዳዎችን ማጠናቀር ሂደት፣ ሥነ ዘዴ እና የተገኙ ውጤቶችን አቅርበው ውይይት የተደረገ ሲኾን፣ በውይይቱ ወቅት የተገኙት ውጤቶች ጥሩ ቢኾኑም የሴቶች ቀዳሚ አጀንዳዎች ቅደም ተከተል ቢከለስ የሚል ሐሳብ ቀርቦ ተቀባይነት በማግኘት በቡድን ውይይት ዳብሮ የመጨረሻ እርማት እንዲደረግ መግባባት ላይ ተደርሷል።

ከዚኹ ጎን ለጎን ጥምረቱ እስካኹን መድረስ ባልቻለባቸው አማራ፣ ትግራይ እና ጋምቤላ ክልሎች ምን ለማድረግ አስቧል የሚል ጥያቄ ተነሥቶ፣ የጥምረቱ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ በተጠቀሱት ክልሎች ተመሳሳይ መድረኮችን ለማድረግ ያሉ የሰላም መደፍረስ ችግሮች እንዳሉ ኾነው፣ ከለጋሾች ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ምላሽ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሳባ ገብረመድኅን፣ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ የተነሣበትን ራእይ ለማሳካት በርካታ ክልሎችን በመሸፈን የሴቶችን አጀንዳዎች ማሰበሰቡ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል። ነገር ግን ሀገራዊ ችግሮች ወንድ፣ ሴት የማይሉ መኾኑን ብሎም የሴቶች ችግሮች በቀላሉ የሚፈቱ ባለመኾኑ በቀጣይ እነዚኽ አጀንዳዎች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ትኩረት እንዲሰጣቸው ለማድረግ በዋናነት የጥምረቱ አባል ድርጅቶች እና ሴቶች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት ጠንካራ የውትወታ ሥራ እንደሚጠብቃቸው አስገንዝበዋል። በሂደቱ ውስጥ ለተሳተፉ ባለድርሻ አካላት፣ ለጋሾች እና አጋሮችም ምስጋና አቅርበዋል።

Share this post on

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *