ሴቶች በሕዝብ አስተያየት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር እንዲችሉ በሕዝብ ፊት የመናገር ችሎታቸውን ማጎልበት ዙሪያ ያተኮረ ሥልጠና ተሰጠ

ትምራን ከፍሪደም ሐውስ (Freedom House) ጋር በመተባበር ለትግራይ ክልል ሴት ፖለቲከኞች እና አመራሮች ለሦስት ቀናት የሰጠችው የተሟጋችነት፣ የተግባቦት፣ በሕዝብ ፊት ንግግር የማድረግ እና የድርድር ክሂሎት ሥልጠና ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ላይ ተጠናቀቀ።

የሥልጠናው የመጨረሻ ቀን ሴቶች ራእያቸውን ለማሳወቅ፣ የሕዝብ አስተያየት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር እና አመኔታን ለማግኘት በሕዝብ ፊት የመናገር ችሎታቸውን ማጎልበት በሚችሉበት ስልት ዙሪያ ያተኮረ ነበረ።

የንግግር ክሂሎትን ለማጎልበት ታዳሚዎችን በሚገባ ማጥናት እና መረዳት፣ ለንግግር የሚሆን ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ ፍርሃትን ለማሸነፍ መሞከር፣ የሰውነት ቋንቋ እና ኢ-ቃላዊ ተግባቦትን መረዳት እንደሚገባ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም የመገናኛ ብዙኀን እና የሕዝብ ትችት አያያዝን በተመለከተ እና በሕዝብ ፊት በሚደረግ ንግግር ወቅት ሊያጋጥም ስለሚችል ጾታን መሠረት ያደረገ መድልኦን መቋቋም በሚቻልበት ርእሶች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል፤ የሥልጠናው ተሳታፊዎችም በዚህ ረገድ ያላቸውን ልምድ አጋርተዋል።

በሥልጠናው ላይ የድርድር መርሆች እና ስልቶች፣ በጾታ ላይ የተመሠረቱ ተግዳሮቶችን ለመወጣት የሚያግዙ ነጥቦች እንዲሁም ለድርድር አስፈላጊ የሆኑ የተግባቦት ስልቶች የሚሉ ጭብጦች ተነሥተዋል።

በመጨረሻም ተሳታፊዎች በተሰጣቸው የመልመጃ ጥያቄ ላይ በመወያየት እና እርስ በእርስ በመደራደር ልምምዶችን አድርገው ከኅዳር 24-26 ቀን 2017 ዓ.ም የቆየው ሥልጠና ተጠናቅቋል።

TIMRAN @5

Share this post on