ትምራን የ2017 ዓ.ም የሥራ ዘመን ጠቅላላ ጉባኤዋን አካሄደች

በተጠናቀቀው ዓመት 5ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሏን ያከበረችው ትምራን የ2017 ዓ.ም የሥራ ዘመን ጠቅላላ ጉባኤዋን መስከረም 10 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ አካሄደች።

ጉባኤተኞችን እንኳን ደኅና መጣችኹ ያሉት የጠቅላላ ጉባኤው ሊቀመንበር መልካምሰው ሰሎሞን፣ በመክፈቻው ላይ የስብሰባውን ምልዓተ ጉባኤ በማረጋገጥ እና የጉባኤውን ርእሰ ጉዳዮች አስጸድቀዋል።

በመቀጠል የትምራን ቦርድ ሰብሳቢ መስከረም ገስጥ፣ በተጠናቀቀው ዓመት ውስጥ በቦርዱ የተከናወኑ ዋና፣ ዋና ጉዳዮችን አቅርበዋል።

ከዚያም የ2017 ዓ.ም ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም በትምራን ጊዜያዊ ሥራ አስኪያጅ ዮዲት ታመነ እንዲሁም ዓመታዊ የሒሳብ አፈጻጸም በሒሳብ ሹሙ ኤልያስ ደበበ እና የዓመቱ ሒሳብ ምርመራ ዘገባ በውጭ ኦዲተር አማካኝነትቀርቦ ውይይት ተደርጎበት በጉባኤው ጸድቋል።

በመጨረሻም የትምራን የ2018 ዓ.ም ዓመታዊ እቅድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ፣ በርካታ ግብአት ከታከለበት በኋላ በሙሉ ድምፅ ጸድቋል።

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ከኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የተወከሉ የሥራ ሓላፊ ውሎውን በተመለከተ ያላቸውን አስተያየት እና ከጉባኤተኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተው ጉባኤው ተጠናቅቋል።  

ትምራን ሴቶች ወደ ፖለቲካ ተሳትፎ እና ውሳኔ ሰጭነት ሚና ውስጥ ወደፊት እንዲመጡ የማስቻል ራእይ ሰንቃ የተቋቋመች ሀገር በቀል ድርጅት በመኾን ላለፉት አምስት ዓመታት በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።  

#TIMRAN@5

Share this post on