የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን ለመምራት የሚወዳደሩ ሴቶች ሐሳቦቻቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት እንዲሁም በሥራ አስፈጻሚነት ለመምራት የሚወዳደሩ ሴቶች ሐሳቦቻቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ታኅሣሥ 02 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተካሄደ።
መርሐ ግብሩ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እና ውሳኔ ሰጭነት ሚና እንዲጎልበት ለማድረግ ዓላማ ሰንቃ በምትንቀሳቀሰው ትምራን የተሰኘች ሀገር በቀል የሲቪክ ማኅበር እና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ትብብር የተዘጋጀ ነው።
በመድረኩ ላይ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የትምራን ቦርድ አባል መስከረም ግርማ፣ ትምራን ላለፉት አምስት ዓመታት ሴቶችን ለአመራርነት ለማብቃት ስትሠራ መቆየቷን ገልጸው፣ የዕለቱ መርሐ ግብር በጥብቅና ሞያ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ለአመራርነት እንዲመረጡ ለማስቻል ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ ነው ብለዋል።
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ኅብረት አባሆይ በበኩላቸው፣ ማኅበራቸው ሴት የሕግ ባለሞያዎችን ከተለማማጅነት ጀምሮ በማሳደግ ለተለያዩ ሓላፊነቶች እንዲበቁ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፣ በመድረኩ ላይ ለዕጩነት የቀረቡት ሴት ተወዳዳሪዎች በኢትዮጵያ የሕግ ሞያ ውስጥ ሴቶችን የማብቃት እንዲሁም ዘርፉ ለወንዶችም፣ ለሴቶችም ምቹ እንዲሆን የማድረግ ሓላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመድረኩ ላይ ቁልፍ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ቦርድ አባል እና የኮቨናንት የጥብቅና ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት ኅትመት አሰፋ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን ለመምራት ወደፊት የመጡ ሴት ጠበቃዎች የሚገጥማቸውን ማንኛውም ውጣ ውረድ አልፈው ለዚህ ደረጃ በመብቃታቸው አመስግነዋል። ለፕሬዚዳትነትም ሆነ ለሥራ አስፈጻሚነት የሚወዳደሩ ተመራጮች በሀገሪቱ የሕግ ዘርፍ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ የማምጣት ሓላፊነት የተጣለባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ለማኅበሩ ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት መሠረት አያሌው እና መሠረት ስዩም እንዲሁም ለሥራ አስፈጻሚነት የሚወዳደሩት ጀሚላ ክብረት፣ ቤዛ ንጉሤ እና ማርያ ካሕሣይ ሐሳቦቻቸውን ለኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አባላት አቅርበዋል።
በፍትሕ ዘርፉ የሴቶች አመራርነት፣ ታማኝነት እና ቁርጠኝነት ሁሉን አካታች የሕግ ከባቢ እንዲኖር በማድረግ ጠንካራ ድምፅ ይፈጥራል።

 

Share this post on