info@timran.et | +251 116 73 48 48
ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲያካሂድ የቆየውን የሴቶች አቅም ግንባታ ሥልጠና አጠናቀቀ


ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲያካሂድ የቆየውን የሴቶች አቅም ግንባታ ሥልጠና ሠኔ 04 ቀን 2016 ዓ.ም አጠናቀቀ። በክልሉ የመጨረሻ ምድብ የነበረውን የጌዲኦ ዞን ሴቶች ሥልጠና በዕለቱ ሰጥቷል።
ጥምረቱ በተለያዩ ክልሎች የሰጣቸው ሥልጠናዎች ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ተገቢ ውክልና እንዲኖራቸው ለማስቻል የተከናወኑ ናቸው።
በጌዲኦ ዞን ዋና ከተማ ዲላ ውስጥ በተሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ላይ ከዞኑ ልዩ፣ ልዩ ወረዳዎች የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የወከሉ 50 ያኽል ሴቶች ተሳትፈዋል።
መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አስቻለው ማቴዎስ፣ ጥምረቱ የተመሠረተበትን ዓላማ እና ያከናወናቸውን ተግባራት ለተሳታፊዎች ገልጸዋል።
አክለውም ጥምረቱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ጨምሮ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲኹም በሐረሪ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ሶማሊ እና ኦሮሚያ በድምሩ በዐሥር ክልሎች ተመሳሳይ የሴቶች አቅም ግንባታ መድረኮች በማዘጋጀት የሴቶችን አጀንዳዎች አሰባስቦ በቅርቡ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይ በማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ አማራ፣ ትግራይ እና ጋምቤላ ተመሳሳይ መድረኮችን የማዘጋጀት እቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።
ተሳታፊዎች ስለ ሀገራዊ ምክክር ምንነት፣ ከሌሎች የግጭት መፍቻ መንገዶች ጋር ስላለው አንድነት እና ልዩነት፣ የምክክር አስፈላጊነት፣ በምክክር ሂደት ውስጥ ሥርዓተ ጾታን የማካተት አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ፣ በምክክር ሂደት ውስጥ የድምፅ አሰጣጥ ዘዴዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ገለጻ ተሰጥቷቸዋል።
ገለጻውን ተከትሎ ከተሳታፊዎች ጥያቄ እና አስተያየት ቀርቦ ምላሽ ከተሰጠ በኋላ ተሳታፊዎች ከሚወክሉት የማኅበረሰብ ክፍል አኳያ ከአካል ጉዳት ጋር የሚኖሩ፣ ወጣቶች፣ የቤት እመቤቶች፣ አርሶ አደሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነጋዴ ሴቶች እና የሴቶች ማኅበራት አባላት በሚሉ ምድቦች ተከፍለው የቡድን ውይይት አድርገዋል።
ከቡድን ውይይት በኋላ ከየምድቡ የተገኙ አምስት፣ አምስት አንኳር አጀንዳዎች በቡድን ተወካዮች በኩል ቀርበው፣ በየፈርጃቸው ተጠቃልለው እና ተነብቦላቸው የጌዲኦ ዞን ሴቶች አጀንዳዎችን በጋራ ድምፅ አጽድቀዋል።
ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ እና አሌ፣ ኮሬ፣ ጋርዱላ እና ቡርጂ፣ አሪ፣ ደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ፣ ሐመር እና ማሌ እንዲኹም ኛንጋቶም፣ ዳሰነች እና ቱርሚ ከተማ አስተዳደር በድምሩ በስምንት ምድቦች ባካሄደው የሴቶች አቅም ግንባታ መድረክ ቁጥራቸው ከ300 በላይ ሴቶች ተሳታፊ ነበሩ።
በተጨማሪም በወላይታ፣ ጋሞ፣ ኮንሶ እና ጋሞ ዞኖች ከራስ አገዝ እንዲኹም በገጠር ቀበሌ ደረጃ ከሚገኙ ሴቶች ጋር አራት የምክክር መርሐ ግብሮች አከናውኗል።
ጥምረቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያካሄዳቸውን የአቅም ግንባታ መርሐ ግብሮች በገንዘብ የደገፈው አየርላንድ ኤምባሲ በአይሪሽ ኤይድ (IRISH AID) በኩል ነው።
ጥምረቱ ባለፉት አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ውስጥ በዐሥር ክልሎች በሰጣቸው የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ከ4000 በላይ ሴቶችን መድረስ ችሏል።