info@timran.et | +251 116 73 48 48
የመካከለኛ ሴት አመራሮች ኅብረት ተወካዮች ከብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ጋር ውይይት አደረጉ


በትምራን አስተባባሪነት የተቋቋመው የመካከለኛ ሴት አመራሮች ኅብረት ተወካዮች ከብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ጋር ሠኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ የኅብረቱ ተወካዮች ከትምራን ጋር በጋራ በመኾን ኅብረቱ የተቋቋመበትን ሴቶች በሰላም ግንባታ ላይ ተገቢ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የማስቻል ዓላማ ለማሳካት የተካሄደ ነው።
የኅብረቱ ተወካዮች ከብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽነሮች ጋር በተነጋገሩበት ወቅት የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ ፈትተው ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ የሴቶች ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተው መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በመካከለኛ አመራርነት ላይ የሚገኙ ሴቶች ኅብረት የተቋቋመው ትምራን በተለያዩ ክልሎች ባካሄደቻቸው የሴቶች የሰላም መድረኮች በመነሣት ሴቶች በሰላም ግንባታ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው የማስቻል ዓላማ ሰንቆ ነው።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 525/2022 የተመሠረተ ሲኾን፣ ኮሚሽኑ በተደራጀ መልክ ሲንቀሳቀስ በነበረ ኃይል ውስጥ ነበሩትን የቀድሞ ተዋጊዎች ከኅብረተሰቡ ጋር በዘላቂነት እንዲዋሐዱ እና ሰላማዊ ሕይወታቸውን እንዲጀምሩ እንዲኹም በሀገሪቱ ልማት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ በመሳተፍ የሚገባቸውን አበርክቶ እንዲወጡ ለማድረግ የሚረዱ ሥራዎችን ለማስተባበር ሓላፊነት ተሰጥቶት የተቋቋመ ነው።