info@timran.et | +251 116 73 48 48
የመካከለኛ አመራር ሴቶች ኅብረት ‘ሴቶች ለሰላም’ በሚል ጭብጥ ለየካ ክፍለ ከተማ ሴቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጠ


በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በትምራን አስተባባሪነት የተቋቋመው የመካከለኛ አመራር ሴቶች ኅብረት ‘ሴቶች ለሰላም’ በሚል ጭብጥ ከየካ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች ለተውጣጡ ሴቶች ያዘጋጀው የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ሠኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሄደ።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የትምራን ፕሮጀክት አስተባባሪ ሰላም ተስፋዬ ትምራን ሴቶች በሀገሪቱ ፖለቲካ እና ውሳኔ ሰጭነት ውስጥ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከአምስት ዓመት በፊት የተቋቋመች የሲቪክ ማኅበር ነች ብለዋል። አያይዘውም ሴቷ ሰላምን ትምራ በሚል ፕሮጀክት በተለያዩ ክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ማካሄዷንና ሰላምን ለማምጣት በሚደረጉ እንደ ሀገራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትሕ የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መኾኗንም ጠቅሰዋል።
በመቀጠል የኅብረቱ አባል የኾኑት ፈትለወርቅ ምትኩ የሰላም ምንነት እና ግጭት፣ የሰላም ምሰሶዎች እና የሴቶች ሚና፣ ሴቶች እና ሰላም በሚሉ ርእሶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ የቅርብ ጦርነት ጋር በተያያዘ በተግባር ያጋጠማቸውን የግጭት ውጤት ለመድረኩ ተሳታፊዎች በተሞክሮነት አቅርበዋል። በዚኽም ከግጭት አትራፊ መኾን እንደማይቻል ተናግረዋል።
ገለጻውን ተከትሎ በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሴቶች ሚና በተመለከተ ለተሳታፊዎች በተሰጠ እድል በርካታ ሐሳቦች ተነሥተዋል። በዋናነት ሴቶች የወንዶችን ተፅዕኖ ተቋቁመው ራስን ለመሪነት ብቁ ለማድረግ መዘጋጀት፣ ከመገፋፋት ይልቅ እርስ በርስ መረዳዳት፣ ሥልጣን ሲያገኙ በአግባቡ መጠቀም፣ መረጃን ከታማኝ ምንጭ መቅዳት፣ የግጭት መንስኤዎች ላይ መነጋገር፣ በማይመለከተን ጉዳይ ውስጥ አለመግባት፣ መተባበር፣ አብሮነትን ማጠናከር እና ልዩነትን አቻችሎ መኖር እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቤተሰብ አገልግሎት እና ማብቃት ሓላፊ የኾኑት ወይንሸት ገለሶ እንዲኹም የብሔራዊ ወጣት ሴቶች በጎ አድራጎት ድርጅት ዳይሬክተር ማርታ ማሙዬ፣ ሴቶች ለሰላም መሠረት መኾናቸውን አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም የትምራን ፕሮጀክት አስተባባሪ ሰላም ተስፋዬ ሰላም ከራስ ይጀምራል በሚል ከተሳታፊዎች የተነሣው ሐሳብ ተገቢነት ያለው በመኾኑ በቀጣይ ሴቶች በተጠናከረ መንገድ ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ አሳስበዋል። ከመረጃ ጋር በተያያዘ ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ከተጠቀምነው እጅግ ጠቃሚ መሣሪያ ነው፤ ስለዚኽ በዕውቀት ላይ በመመሥረት መረጃን አጣርቶ መጠቀም አስፈላጊነቱን ጠቅሰው ለተሳታፊዎች ምስጋና በማቅረብ መድረኩ ተጠናቅቋል።